Romans 2

የእግዚአብሔር ጻድቅ ፍርድ

1ስለዚህ አንተ በሌላው ላይ የምትፈርድ፣ የምታመካኝበት የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር ሁሉ፣ ራስህን ትኰንናለህ፤ ፈራጅ የሆንኸው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። 2እንደዚህ በሚያደርጉትም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ ትክክለኛ መሆኑን እናውቃለን። 3እንግዲህ አንተ ሰው በሌሎች ላይ እየፈረድህ ያንኑ የምታደርግ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃል? 4ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ?

5ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን በራስህ ላይ ቍጣን ታከማቻለህ። 6እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”። 7በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። 8ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል። 9ክፉ በሚያደርግ በማንኛውም ሰው፣ አስቀድሞ በአይሁድ ከዚያም በአሕዛብ ላይ መከራና ጭንቀት ይሆናል፤ 10ነገር ግን በጎ ለሚሠራ ለማንኛውም፣ አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ይሆንለታል፤ 11እግዚአብሔር ለማንም አያደላምና።

12ሕግ ሳይኖራቸው ኀጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኀጢአት የሠሩ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ 13ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሚባሉት ለሕጉ የሚታዘዙ እንጂ፣ ሕጉን የሚሰሙ አይደሉም። 14ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። 15ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከስሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ። 16ይህም በወንጌል እንደማስተምረው እግዚአብሔር በሰው ልብ የተሰወረውን በክርስቶስ በኩል በሚፈርድበት ዕለት ግልጽ ይሆናል።

ሕግና አይሁድ

17አንተ ይሁዲ ነኝ ካልህ፣ በሕግ የምትተማመንና ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ግንኙነት የምትኵራራ፣ 18በሕግ በመመራትህም ፈቃዱን ዐውቀህ ፍጹም የሆነውን ለይተህ ከያዝህ፣ 19ለዕውሮች መሪ፣ በጨለማ ላሉትም ብርሃን መሆንህን ርግጠኛ ከሆንህ፣ 20በሕጉም ካገኘኸው ዕውቀትና እውነት የተነሣ አላዋቂ ለሆኑት መካሪ፣ ለሕፃናት አስተማሪ ከሆንህ፣ 21እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን? 22አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን? አንተ ጣዖትን የምትጸየፍ፣ ቤተ መቅደስን ትመዘብራለህን? 23አንተ በሕግ የምትመካ፣ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታዋርዳለህን? 24ይህም “በእናንተ ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ ይሰደባል” ተብሎ እንደ ተጻፈው መሆኑ ነው።

25ሕግን የምትፈጽም ከሆነ ግዝረት ዋጋ አለው፤ ሕግን የምትተላለፍ ከሆነ ግን እንዳልተገረዝህ ትሆናለህ። 26ያልተገረዙት ሕጉ የሚያዝዘውን የሚፈጽሙ ከሆነ፣ እንደ ተገረዙ አይቈጠሩምን? 27አንተ የተጻፈ ሕግ፣ ግዝረትም ቢኖርህ፣ ሕግ ተላላፊ በመሆንህ፣ በሥጋ ያልተገረዘው ለሕግ በመታዘዙ ይፈርድብሃል።

28አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊው ብቻ ይሁዲ ልሁን ቢል ይሁዲ አይሆንም፤ እውነተኛ ግዝረትም ውጫዊና ሥጋዊ ሥርዐት አይደለም። 29ዳሩ ግን አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

Copyright information for AmhNASV